ውብሸት ሰንደቁ
ከጎጆ ኢንዱስትሪ ተነስቶ ራሱን በራሱ እያስተማረና እያሳደገ የመጣ ድርጅት ነው። መጀመሪያ በጎጆ ኢንዱስትሪ ደረጃ በ1979 ዓ.ም ጥቂት ሰዎችን በመቅጠርና ሰንደል በማምረት ተጀመረ። በውስጡ ምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ ሂደት ሳይኖረው በእጅ በሚከናወኑ ተግባራት ምርት ያመርት ነበረ። ቀርከሃ።
ከሰል ዱቄት እና ከውጪ ይመጣ የነበረ ለማጣበቂያነት የሚውል ቅርፊት ዱቄት የነበሩ ግብዓቶችን ሴቶች በተርታ ተቀምጠው ሂደቱን በመጠበቅ በቅብብሎሽ ነው ጀማሪው ኢንዱስትሪ ሰንደል ያመርት የነበረው።
ከዚህ በጀመረው የቀርከሃ ትውውቅ ዛሬ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በፋብሪካ ደረጃ የሚሠራቸው የቀርከሃ ምርቶች በርካታ ሆነዋል። ከተረፈ ምርቱ ተቀምመው ደግመው ለፋብሪካው ግብዓት የሚውሉትን ምርቶች ሳይጨምር ኢንዱስትሪው ከቀርከሃ ፐልፕና ወረቀት።
አምሥት ማዕዛቸው የሚለያይ ለ35 ዓመታት በምርት ላይ የቆዩ የሰንደል ምርቶች። በነጠላ የታሸገ የጥርስ ቆሻሻ ማውጫ (ስቴክኒ)። የቀርከሃ መጋረጃ እና የገበታ ማስቀመጫ። ለወለል ምንጣፍ እና ለኮርኒስ የሚያገለግል የቀርከሃ ጣውላ ያመርታል።
ይህ ድርጅት አዳአል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይሰኛል፤ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጁ ደግሞ አቶ አዳነ በርሄ ናቸው። አቶ አዳነ የኢንዱስትሪውን ጓዳ ስንቃኝ እንዲህ ብለውናል፤ የቀርከሃ ሥራን ከጀመርኩ በኋላ ሌሎች እሠራቸው የነበሩ ሥራዎችን በሙሉ አቁሜ ሥራውን በፍቅር መሥራትን ተያያዝኩት። በወጣትነቴ በመጀመሬ የፈጠራ ችሎታውም ጉልበቱም ስለነበረኝ ከጎጆ ኢንዱስትሪ የተነሳው አሁን ላይ በርካታ የምርት ዓይነቶችን ማምረት የሚችል ኢንዱስትሪ መሆን ችሏል።
ከዋና ዋና ምርቶች አንፃር ከታየ አምሥት ፋብሪካ ሊከፍት የሚያስችል ድርጅት ሆኗል።
አቶ አዳነ እንደነገሩን ሥራው በተጀመረበት ወቅት ሀገሪቱ ትከተለው በነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብዙ ማደግና ከተወሰነ የካፒታል አቅም በላይ መሄድ አይፈቀድም። በወቅቱ ከ500 ሺህ ብር ካፒታል ለድርጅትም ሆነ ለግል ተቋም ባይፈቀድም ኢንዱስትሪ ካላደገ የሥራ ባህልም ሆነ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊያድግ እንደማይችል የተረዱት እኒህ ቆራጥ ሰው ያልሙት የነበረውን ኢንዱስትሪ በጎጆ ኢንዱስትሪነት ጀምረው በመታተር ለዚህ ማብቃት ችለዋል።
ለኢንዱስትሪዎች ማደግ የመንግሥት ፖሊሲዎች የማዕዘን ድንጋይ ሆነው ያገለግላሉ። እናም በዚያ ወቅት አሣሪ የነበሩ አሠራሮች በ1983 የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የነፃ ገበያ ተጀመረ። ነፃ ገበያውን ተከትሎ የጥራት ውድድር ማድረግ ቀጠለ። የነበረው ለውጥ ሂደታዊ ስላልነበረ የግል ዘርፉ በወቅቱ በጥራት አምርቶ በውድድር የመሸጥ ልምምድ አልነበረውም። በመሆኑም በወቅቱ ኢትዮጵያ ለሌሎች የቅርብና የሩቅ ሀገራት እንደሸቀጥ ማራገፊያ ሆነች።
አቶ አዳነ በጊዜው ዓለምን የሚመጥን ጥራት ይዘው ማምረት ባለመጀመራቸው የሚያመርቱት ምርት ተወዳዳሪ ሊሆን አልቻለም፤ በዚህ ምክንያትም ከገበያ ልንወጣ ተገደድን ይላሉ። በወቅቱ የነበረው አማራጭ ገበያውን ተቆጣጥሮ የነበረውን ዓይነት ምርት በጥራትና በብዛት ማምረት መቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ ይል ነበር። ለዚህ ሲባል በቴክኖሎጂ በመታገዘ ሰንደል ያመርቱ ወደ ነበሩ ሀገራት ማለትም ወደሩቅ ምሥራቅ በመሄድ ልምድ ቀስመው ተመለሱ።
ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ የግብዓት ዓይነትና ጥራት። የቴክኖሎጂውን ዓይነትና ዘዴውን ቀይረው ለገበያውን ፍላጎት በተወዳዳሪነትና በጥራት ማቅረብ ጀምረው ወደገበያ ገብተዋል። በዚህ ጊዜ የሰው ኃይሉም ወደ 80 ሰው ከፍ እንዳለ ይናገራሉ።
በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ ወደ ታይዋንና ቻይና ተመልሰው በመሄድ የቀርከሃን ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ በማየት አቅም የፈቀደውን ቴክኖሎጂ በማምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ በነጠላ የታሸገ የጥርስ ቆሻሻ ማስወገጃ ስንጥር (ስቴክኒ) ማምረት ጀመሩ።
ከዚህ በመቀጠል የቀርከሃ ጣውላና የቀርከሃ መጋረጃ፤ ከተረፈ ምርቱ ደግሞ ጭስ አልባ ከሰል ማምረት ጀምረዋል።
ድርጅቱ እስካሁን ድረስ የዓለም የቀርከሃ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ በመከተል የምርት ቱርፋቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማቅረቡን እንደቀጠለ መሆኑን ያስረዳሉ። ለማሳያም አሁን የቀርከሃ ፐልፕ (የወረቀት ምርት ዋና ግብዓት) እና ወረቀት ማምረት የሚችለውን ቴክኖሎጂ አስመጥተው በቅርቡ ወደሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ። ከቀርከሃ ፐልፕ በማውጣትም ለወረቀት ፋብሪካዎች መስጠትም ጀምረዋል።
በዓለም ላይ የቀርከሃ ፐልፕ መሥራት የሚችሉት ጥቂት ኢንዱስትሪዎች ናቸው የሚሉት አቶ አዳነ በአፍሪካ ይሁን በኢትዮጵያ ደረጃ ከቀርቀሃ ፐልፕ ማምረት የእርሳቸው ኢንዱስትሪ የመጀመሪያው እንደሆነና በዚህም ኩራት እንደሚሰማቸው ይገልፃሉ።
ይሁን እንጂ መንግሥት ለቀርከሃ ምርት ትኩረት ሰጥቷል የሚል እምነት የላቸውም። በሌሎች ሀገሮች እንደብራዚል። ህንድ። ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ዘርፉ እንደዘርፍ አልተመዘገበም። አሥረጅ ይሆን ዘንድም የቀርከሃ ሥራ እየሠሩ መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው የግንድና ጣውላ ንግድ የሚል ነው።
በዘርፉ ጎልቶ የሚታየው ተሥፋና ተግዳሮት ምንድን ናቸው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንደ መልካም አጋጣሚ የጠቀሱት ነፃ ገበያና የኢኮኖሚ ፖሊሲውን ነው። ተግዳሮት በማለት ያነሱት ደግሞ እነዚህ ፖሊሲዎች። ደንብና መመሪያዎችን ተግባራዊ የሚያደርግ የመንግሥት ተቋም በአግባቡ መሥራት አለመቻላቸውን ነው።
ይህም ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል። በተጨማሪም አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ከለውጡም በኋላ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ያላቸው አመኔታ ዝቅተኛ መሆን መታረም ያለበት ትልቅ ተግዳሮት ነው በማለት ጠቅሰዋል።
አዳአል ኢንዱስትሪያል በአሁኑ ጊዜ ለ220 ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን የቀርከሃ ምርቶቹን ወደግብፅ። ሕንድና ሊባኖስ መላክ ጀምሯል፤ ወደተጨማሪ ሀገሮችም ለመላክ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ኢንዱስትሪ ነው። በዋጋና በብዛት ምርትን በማቅረብ ረገድ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ምርቶቹ ጥሩ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ከድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ መረዳት ችለናል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013